የኦዲት ግኝት ባለድርሻ አካላት የትብብር ፎረም የ2010 በጀት አመት እንቅስቃሴ ከቀደሙት አመታት የተሻለ ስራ የተሰራበት እንደነበረ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የጋራ ፎረሙ የ2010 እቅድ አፈጻጸሙን ሰኔ 27/2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ በገመገመበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ ቋሚ ኮሚቴውና የፎረሙ አባል መስሪያ ቤቶች በ2010 በጀት አመት ባዘጋጁት የጋራ እቅድ መሰረት በይፋዊ ህዝባዊ የስብሰባ መድረኮችና በመስክ ጉብኝቶች ከቀድሞው የተሻሉ ቅንጅታዊ የክትትል፣ ቁጥጥርና የድጋፍ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡

የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት በ2010 በጀት አመት የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ስራዎች የተገኙ ዋና ዋና ውጤቶችን የታዩ ዋና ዋና ጥንካሬዎችንና መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮችን በማስመልከት በቋሚ ኮሚቴው የተደረገውን ግምገማ መሰረት ያደረገ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ለባለድርሻ አካላቱ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው፣ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና በባለድርሻ አካላት እቅድ ታቅዶና የጋራ ተደርጎ ወደስራ በመገባቱ የቅንጅት አሰራሩ እየተጠናከረ መምጣቱ እንዲሁም የኦዲት ግኝቶች በምክር ቤቱ ውስጥ እና ከምክር ቤቱ ውጪ ኃላፊነት ባለባቸው አካላት ዘንድ አጀንዳ ማድረግ መቻሉና በዚህም የኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ የማይወስዱ አስፈጻሚዎች በኃላፊነት መቆየት የሚችሉበት ስርአት እንደማኖር በመንግስት በኩል እንደ አንድ መስፈርት መታየቱ ከተገኙ ውጤቶች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

በጋራ ፎረሙ እንቅስቃሴ ከታዩ ጥንካሬዎች ውስጥ አብዛኞቹ የፎረሙ አባላት በቅንጅት የሚፈጽሟቸውን የየራሳቸውን ተግባራት ለይተው ዝርዝር እቅድ በወቅቱ አዘጋጅተው ለቋሚ ኮሚቴው መላካቸውና ወቅታዊ ሪፖርቶችንም ማቅረባቸው፣ ሊደረጉ ከታቀዱ 21 ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባዎች ውሰጥ 18 መካሄዳቸው፣ በመድረኮቹም ላይ አብዛኞቹ ባለድርሻ አካላት በመገኘት ስለ ኦዲት ተደራጊዎቹ መረጃዎችን በመስጠትና መወሰድ ባለባቸው የእርምት እርምጃዎችና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ አስተያየት በማቅረብ ገንቢ ሚና መጫወታቸው ተጠቅሷል፡፡

የመስክ ጉብኝቶችን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በአግባቡ ተከታትሎ በማካሄድ በኩል ቋሚ ኮሚቴው ያደረገው ጥረትና ባለድርሻ አካላትም በጉብኝቶቹ በመሳተፍ ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ግኝት መሰረት ተጠያቂነትን ለማምጣት ለሚሰራው ክትትልና ግምገማ ድጋፍ ማድረጋቸውም በጥንካሬ ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በይፋዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት በኦዲት አስተያየት መሰረት የተቋማት እርምጃ አወሳሰድ ላይ የማረጋገጫ አስተያየት በመስጠትና ቋሚ ኮሚቴው ተጨማሪ መረጃ ሲፈልግ በመላክና ማብራሪያም ሲጠየቅ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ኃላፊነቱን መወጣቱ በጥንካሬ ተጠቅሷል፡፡

እንደዚሁም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለቋሚ ኮሚቴውና ለሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎችና ምክትል ሰብሳቢዎች ለክትትልና ቁጥጥር ስራ የሚያግዛቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱ እንዲሁም በመ/ቤቱ የ2008 በጀት አመት ኦዲት ግኝት መሰረት ኦዲት በተደረጉ መ/ቤቶች በኩል የተደረጉ የማስተካከያ እርማጃዎች ላይ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በኩል የክትትል ኦዲት ተደርጎ ለኮሚቴው የተላከው ሪፖርት ለክትትልና ቁጥጥር ስራ አጋዥ ሆኖ ማገልገሉ በጥንካሬ ተነስተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትንና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርን ለአብነት በመጥቀስ አንዳንድ ባለድርሻ አካላት በተለይም የተቆጣጣሪነት ስልጣን ያላቸው ተቋማት ከኦዲት ግኝት ማሻሻያ እርምጃ አወሳሰድ ጋር ተያይዞ በራሳቸው መ/ቤት ራሱን የቻለ መድረክ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በማዘጋጀት የተለያዩ ስራዎችን መስራታቸውም በጥንካሬ ታይቷል፡፡

በአንጻሩ አንዳንድ ተቋማት በራሳቸው ደረጃ የሚከናወኑ ተግባራትን ለይተው ያላሳወቁ መሆኑ እንዲሁም በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማት በህዝባዊ ይፋዊ ስብሰባዎች ላይ አለመገኘታቸው፣ አንዳንድ ባለድርሻ አካላት አልፎ አልፎ ስለ ኦዲት ተደራጊው መ/ቤት የተሟላ መረጃ ሳይዙ መቅረባቸው፣  መሻሻል የሚፈልጉ ጉዳዮች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንደዚሁም አንዳንድ መ/ቤቶች በይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ወቅት ከቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከባለድርሻ አካላት የሚሰጣቸውን አስተያየትና አቅጣጫ እንዲሁም በዋና ኦዲተር መ/ቤት የተሰጣቸውን የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየት በአዎንታ ተቀብለው ወደ ስራ በመግባት በኩል አሁንም ጉድለት ያለባቸው በመሆኑ በዚህ ረገድ በጋራ ፎረሙ አባላት በኩል አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ተጠያቂነትን ለማምጣት የተደረገው ክትትልና ቁጥጥር በቂ አለመሆኑ በተለይ ደግሞ የተቆጣጣሪነትና ህግ የማስከበር ስልጣን ያላቸው ምክር ቤቱ እና ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲሁም ሌሎች አካላት ጉድለት የታየባቸው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በእቅድ ግምገማ መድረኩ ወቅት ኦዲት ተደራጊ ተቋማትን በተመለከተ ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ አብዛኞቹ የኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች ከኦዲቱ በኋላ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የድርጊት መርሀ ግብር ቢያዘጋጁም ከተወሰኑ መ/ቤቶች በቀር በድርጊት መርሀ ግብሩ መሰረት እርምጃ የማይወስዱ መሆኑ፣ የወሰዷቸው እርምጃዎች ሲኖሩም ለሚመለከታቸው አካላት በወቅቱ ትኩረት ሰጥተው የማያሳውቁ መሆናቸው ተነስቷል፡፡

ከዚህ ሌላም ሁሉም ችግሩ ያለባቸው መ/ቤቶች የሂሳብ ኦዲት ግኝቶችን በዋና ኦዲተሩ አስተያየት መሰረት በተሟላ መልኩ ለመፈጸም የሚያሳዩት ቁርጠንነት አናሳ መሆኑ፣ የተቋማቸውን የውስጥ ኦዲት የስራ ክፍል ፋይዳ በመረዳት በአደረጃጀትና በሰው ሀይል በተገቢው ሁኔታ ከመደገፍ አንጻር ውስንነት መኖሩ ተገልጿል፡፡

የክዋኔ ኦዲት ግኝቶችንም ከማረም አንጻር ድክመት ያለ መሆኑና ተቋማት በቂ የስጋት ተጋላጭነት የዳሰሳ ጥናት ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት የማይተገበር በመሆኑ የሚጀመሩ የተለያዩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጭምር በተያዘላቸው ጊዜና ገንዘብ የማይጠናቀቁ ብሎም የሚቋረጡ መሆኑ  ተጠቅሷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የክትትልና ቁጥጥር ስራውም ሆነ ቅንጅታዊ አሰራሩ ድክመት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይም ከአመት አመት በሚመጡ ግኝቶች ላይ የመጨመር እንጂ የመሻሻል አዝማሚያ እምብዛም የማይታይ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባም ሆነ የመስክ ጉብኝት ምልከታ፣ ክትትልና ቁጥጥር እንደታየና የመጠን ለውጥ ካልሆነ በስተቀር ከችግሮች ነጻ የሆነ የመንግሰት ተቋም የሌለ መሆኑ ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡

በቀጣይ የባለድርሻ አካላት የጋራ ፎረም ዋና የትኩረት አቅጣጫ  የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባቀረበው የ2009/20010 የኦዲት ሪፖርት ሂሳባቸው የጎላ ችግር ያለበት 53 ተቋማትንና የኦዲት አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸውን 8 ተቋማት ካሉበት ደረጃ እንዲወጡ ማገዝ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

በዚህ ሂደትም በተለይ የተጠራቀሙ ተሰብሳቢ ሂሳቦች መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም ተደጋጋሚ ግኝት እንዳይኖር አስፈላጊው የህግና የአሰራር ማሻሻያ እንዲደረግ ድጋፍ ማድረግ እንደሚተኮርባቸው ተገልጿል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከናወኑት ተግባራት በአራት እንደተከፈሉ የተገለጸ ሲሆን እነርሱም አስተዳደራዊ መፍትሄ መስጠት፣ ግኝት እንዳይኖር   የህግና አሰራር ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ የፍትሀ ብሄር ክስ በሚያስፈልጋቸው ላይ ክስ መመስረት እንዲሁም ወንጀል ነክ ባህሪ ባላቸው ግኝቶች ላይ የወንጀል ክስ መመስረት እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከነዚህ ውጪም የተቋማት የፋይናንስ ሀብት አስተዳደር አፈጻጸም ላይ የተሞክሮ ልውውጥ መድረክ  ማካሄድ መታቀዱ ተገልጿል፡፡

እነዚህን ተግባራት ለማሳካትም የፎረሙ አባላት የተናጠልና የጋራ ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው የተገለጸ ሲሆን የመድረኩ ባለድርሻ አካላት የቀጣይ በጀት አመት እቅዳቸውን አዘጋጅተው እንዲልኩ ተጠይቋል፡፡

የጋራ ፎረሙ አባላት በበጀት አመቱ በጋራና በተናጥል የተሰሩ ስራዎች በመነሻ የውይይት ሰነዱ የተጠቀሱትን መልካም ውጤቶችን እያስገኙ እንዳለና መጠናከር እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን በዚህ በኩል በቀጣይ ሊሰሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አስተያየት በመስጠት ውይይት አድርገዋል፡፡